Wednesday, May 13, 2009

ሥነ - ፅሁፍን በጥቂቱ

በሥነ - ፅሁፍ ዓለም ግጥም፣ አጭር ልብ ወለድ፣ ረጅም ልብ ወለድ፣ ታሪክ፣ ግለ ታሪክ . . . እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ልብ ወለድ - ረጅም ልብ ወለድ እና አጭር ልብ ወለድ በሚል በሁለት ይከፈላል። አጭር ልብ ወለድና ረጅም ልብ ወለድን «እንጀራ» እና «እንጎቻ» ብለው የሚገልፁት አሉ። ከመጠን መበላለጥ በቀር አገልግሎቱ፣ ጥሬ እቃው፣ አሰራሩ ተመሳሳይ ነው እንደማለት።
አጭር ልብ ወለድ እንደ ረጅም ልብ ወለድ ሁሉ፤ ታሪክ፣ ገፀ ባህሪያት፣ መቼት፣ ምክንያት እና ውጤት . . . የመሳሰሉትን አላባውያን ይጋራሉ። በርግጥ አጭር ልብወለድ እና ረጅም ልብ ወለድ የየራሳቸው የሚለያዩበት መንገድ አለ።
ለምሳሌ ያህል አጭር ልብ ወለድ በጥድፊያ የተሞላ ነው፤ ረጅም ልብ ወለድ ግን ታሪኩን ጥግ ወስዶ የመመለስ፤ ሽቅብ ቁልቁል የማገለባበጫ ግዜ አለው።
አጭር ልብ ወለድ ላይ የገፀ ባህሪያቱን ቁመናና ዛላ ለመግለፅ፣ ከልደት እስከ ሞት ያለውን ታሪካቸውን ወይም የህይወት ገጠመኛቸውን መተረክ አይችልም። በተቃራኒው ረጅም ልብ ወለድ ከአነጋገር ጀምሮ፣ አበላልና አረማመድ፤ ምን ይወዳል? ምን ይጠላል? መቼ? የት? ከማን ተወለደ? እናትና አባቱ፣ እህት ወንድሞቹ፣ ጓደኞቹ . . . ልጆቹ እነማን ናቸው? ምን አሉ? የሚለውን የመተንተን ሙሉ ነፃነት አለው።
በሌላ በኩል ግን አጭር ልብ ወለድ ላይ የተቀመጠው እያንዳንዱ ነገር ታሪኩ ከመጠናቀቁ በፊት መፈንዳት አለበት፤ የሥነ ጽሁፍ መጽሃፍት እንደሚሉት «ግርግዳው ላይ የተሰቀለው ጠመንጃ ታሪኩ ከመጠናቀቁ በፊት መተኮስ አለበት»። ይህም ማለት አላስፈላጊ ቃላት፣ ገለፃ፣ ውጤት የማያስገኝ ገፀ ባህሪ፣ ለታሪኩ አጨራረስ የማያስፈልጉ ግዜና ቦታዎች . . . በታሪኩ ውስጥ ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም። አጭር ልብ ወለድ ነጠላ ውጤት አለው፡፡
ረጅም ልብ ወለድ ግን ምክንያት እና ውጤት እየተቀጣጠሉ . . . አዳዲስ ገፀ ባህርያት እና ታሪኮችን በመጨማመር የሚያድግ ሲሆን ለታሪኩ መበልፀግ የሚበጁ አዳዲስ ገፀ ባህርያትና ታሪኮች፤ እየተነሱ ይወድቃሉ፤ ታይተው ይከስማሉ።
በባህሪያቸው ተመሳሳይ የሆኑት አጭር ልብ ወለድና ረጅም ልብ ወለድ የየራሳቸው የአፃፃፍ ቴክኒክና ተደራሲ አላቸው።ታሪክና ግለ ታሪክም እንደዚሁ እውነተኛ ገፀ ባህሪ፣ ታሪክና መቼት /ቦታና ግዜ/ ይኖራቸዋል። ታሪኩን ይዘው የሚነጉዱ፣ መፅሃፉን የሚያዳብሩ ታሪክና ገጠመኞች ይተረኩበታል፤ አንባቢን እንዳይሰለቸውም የተለያዩ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮችንና ገጠመኞችን በመጨማመር ታሪኩን ማዳበር ይቻላል።