Wednesday, May 13, 2009

ሥነ - ፅሁፍን በጥቂቱ

በሥነ - ፅሁፍ ዓለም ግጥም፣ አጭር ልብ ወለድ፣ ረጅም ልብ ወለድ፣ ታሪክ፣ ግለ ታሪክ . . . እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ልብ ወለድ - ረጅም ልብ ወለድ እና አጭር ልብ ወለድ በሚል በሁለት ይከፈላል። አጭር ልብ ወለድና ረጅም ልብ ወለድን «እንጀራ» እና «እንጎቻ» ብለው የሚገልፁት አሉ። ከመጠን መበላለጥ በቀር አገልግሎቱ፣ ጥሬ እቃው፣ አሰራሩ ተመሳሳይ ነው እንደማለት።
አጭር ልብ ወለድ እንደ ረጅም ልብ ወለድ ሁሉ፤ ታሪክ፣ ገፀ ባህሪያት፣ መቼት፣ ምክንያት እና ውጤት . . . የመሳሰሉትን አላባውያን ይጋራሉ። በርግጥ አጭር ልብወለድ እና ረጅም ልብ ወለድ የየራሳቸው የሚለያዩበት መንገድ አለ።
ለምሳሌ ያህል አጭር ልብ ወለድ በጥድፊያ የተሞላ ነው፤ ረጅም ልብ ወለድ ግን ታሪኩን ጥግ ወስዶ የመመለስ፤ ሽቅብ ቁልቁል የማገለባበጫ ግዜ አለው።
አጭር ልብ ወለድ ላይ የገፀ ባህሪያቱን ቁመናና ዛላ ለመግለፅ፣ ከልደት እስከ ሞት ያለውን ታሪካቸውን ወይም የህይወት ገጠመኛቸውን መተረክ አይችልም። በተቃራኒው ረጅም ልብ ወለድ ከአነጋገር ጀምሮ፣ አበላልና አረማመድ፤ ምን ይወዳል? ምን ይጠላል? መቼ? የት? ከማን ተወለደ? እናትና አባቱ፣ እህት ወንድሞቹ፣ ጓደኞቹ . . . ልጆቹ እነማን ናቸው? ምን አሉ? የሚለውን የመተንተን ሙሉ ነፃነት አለው።
በሌላ በኩል ግን አጭር ልብ ወለድ ላይ የተቀመጠው እያንዳንዱ ነገር ታሪኩ ከመጠናቀቁ በፊት መፈንዳት አለበት፤ የሥነ ጽሁፍ መጽሃፍት እንደሚሉት «ግርግዳው ላይ የተሰቀለው ጠመንጃ ታሪኩ ከመጠናቀቁ በፊት መተኮስ አለበት»። ይህም ማለት አላስፈላጊ ቃላት፣ ገለፃ፣ ውጤት የማያስገኝ ገፀ ባህሪ፣ ለታሪኩ አጨራረስ የማያስፈልጉ ግዜና ቦታዎች . . . በታሪኩ ውስጥ ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም። አጭር ልብ ወለድ ነጠላ ውጤት አለው፡፡
ረጅም ልብ ወለድ ግን ምክንያት እና ውጤት እየተቀጣጠሉ . . . አዳዲስ ገፀ ባህርያት እና ታሪኮችን በመጨማመር የሚያድግ ሲሆን ለታሪኩ መበልፀግ የሚበጁ አዳዲስ ገፀ ባህርያትና ታሪኮች፤ እየተነሱ ይወድቃሉ፤ ታይተው ይከስማሉ።
በባህሪያቸው ተመሳሳይ የሆኑት አጭር ልብ ወለድና ረጅም ልብ ወለድ የየራሳቸው የአፃፃፍ ቴክኒክና ተደራሲ አላቸው።ታሪክና ግለ ታሪክም እንደዚሁ እውነተኛ ገፀ ባህሪ፣ ታሪክና መቼት /ቦታና ግዜ/ ይኖራቸዋል። ታሪኩን ይዘው የሚነጉዱ፣ መፅሃፉን የሚያዳብሩ ታሪክና ገጠመኞች ይተረኩበታል፤ አንባቢን እንዳይሰለቸውም የተለያዩ ልብ አንጠልጣይ ታሪኮችንና ገጠመኞችን በመጨማመር ታሪኩን ማዳበር ይቻላል።



Thursday, April 30, 2009

የአማሪኛ ስነ ፅሁፍ ታሪክ

በኢትዮጵያ የስነ ፅሁፍ ታሪክ አማርኛ ቋንቋ ረጅም እድሜን አስቆጥሯል። በድንቅ ጥበባቸው ከሚደነቁት «ፍቅር እስከ መቃብር»፣ «ከአድማስ ባሻገር»፣ «አደፍርስ» … እና ሌሎችም ድርሰቶች ባሻገር ዘመን የማይሽራቸው በርካታ መፅሃፍትን አንብበናል፤ ወደፊትም እናነባለን።የዛኑ ያህልም ከደራሲው እና አሳታሚው በቀር ማንም ያላያቸው፤ ለንባብ የማይጋብዙ፤ ለደራሲውም ሆነ ለአሳታሚው ኪሳራ የሆኑ መፅሃፍትም አሉ። መፅሃፍት ብቻ አይደሉም ሌሎች የስነ ጥበብ ስራዎች፤ አንድ ደራሲ ከመፃፉ በፊት «ምን ማድረግ አለብኝ» የሚለውን ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ ይገባዋል። ከባለሙያዎች ጋርም የሚመካከርበት ጊዜ ያስፈልገዋል።መፅሃፍ «እነ እገሌ ፅፈዋልና ልፃፍ…» ተብሎ የሚፃፍ፤ «ጥሩ ገጠመኝ አለኝ» … አለያም «ታሪክ አውቃለሁ» ተብሎ የሚጀመር፤ ገንዘብ ስላለም እንዲሁ ለህትመት የሚበቃ መሆን የለበትም። ወረቀት የያዘውን ታሪክ ይይዘዋል፣ ወረቀት የያዘው አይረሴ ነው… ስምን ዘልአለም የሚያስነሳ… በመልካምነቱ የሚያስወድስ… በብቃት ማነሱ ደግሞ የሚያስወቅስ ሆኖ ይኖራል።በመሆኑም የመፃፍ አላማ ያለን … እንደ ወደፊት እቅዳችን የያዝን … መፃፍ የጀመርን እና ማጣፊያው ያጠረን፣ መፅሃፋችን የሚነበብ እንጂ የሚቀመጥ እንዳይሆን፤ ታሪክ የሚያነሳው፣ ለኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ አንድ ነገር የሚጨምር . . . አንድ እርምጃ የሚያስኬድ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ከወዲሁም መዘጋጀት ይጠበቅብናል።በጋዜጠኝነት የሥራ ዘመኔ ከነበረኝ ገጠመኝ አንዱን ላውጋችሁ። አንድ ራሱን ደራሲ ብሎ የሚጠራ ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ ከአንድ የጋዜጣ አርቲክል ልትዘል የማትችልን ፅሁፍ ሁሉ በድፍረት የሚያሳትም ግለሰብ ነው። ደራሲ መባል ካለው ጉጉት በተጨማሪ CVዬን ይገነባልኛል በሚል ብቻ ይፅፋል ያሳትማል። እንዲሻሻጥለት ደግሞ ጋዜጦች ጋር እየሄደ ስራዎቹን የሚያወድስ ፅሁፍ እንዲወጣ ይጠይቃል። እንደውም በብዕር ስም እየፃፈ መወድሱን በጋዜጣ ለማሳተም ጥረት ያደርጋል። ይህን ግለሰብ በዚህ አጋጣሚ ነበር የተዋወቅኩት። ቅር ካላለኝ ያመጣውን «መወድስ» እንዳለ በጋዜጣው ኪነ ጥበብ ገፅ ላይ እንዲታተምለት፣ ማየት ከፈለኩ ግን መፅሃፉን እንዳነብ ጋበዘኝ፤ በርግጥም ከፍተኛ አድናቆት የተቸረውን መፅሃፍ ለማንበብ ጓጓሁ፣ ከነበአሉ ግርማ ስራ ቀጥሎ የሚመደብ የተባለለትን መፅሃፍ አነበብኩት፤ ተሳስቼ ከሆነ ብዬም ለተለያዩ የስነ ፅሁፍ ተማሪዎችና ባለሙያዎች በግሌ አሳየሁ።የሁላችንም አስተያየት ግን አንድ ነበር . . . አማካሪ ቢያገኝ ከመፅሃፍት ተራ የማይሰለፍ! የፅሁፉ አቅራቢም ደራሲ መባል የማይገባው! እንደውም በአንዳንዶች አገላለፅ ድርሰት እንዴት መፃፍ እንደሌለበት የሚያስረዳ!ይህንኑ የሌሎችና የራሴን ምልከታ ነበር በጋዜጣው ላይ ያተምኩት። በማግስቱ ታዲያ ብስጭቱን በቀላሉ መግለፅ የማይቻል . . . ለገላጋይ ያቃተ «ደራሲ»፤ «ስሜ እንደጠፋ ህይወት አጠፋለሁ» ከሚል ግለሰብ ጋር ነበር የተጋፈጥኩት።እንዲህም ይፃፋል ልላችሁ ነው። አንዳንድ ግዜ ስመለከት የህይወት ገጠመኜ ለራሴ አስደምሞኛል በሚል ብቻ መፅሃፍ ሲሆን ይስተዋላል። ጥሩ ባለሙያ ቢያገኝ ምርጥ ስራ ሊሆን የሚችል ታሪክ ደግሞ እንዲሁ ተድበስብሶ ሲቀር ይስተዋላል።ለዚህ መድሃኒቱ ደግሞ ከባለሙያ ጋር መመካከር ነው። አጠገብ ያለ ጓደኛ ወይም ቤተሰብም እኮ ጥሩ ምክር ይለግሳል። ባወጣ ያውጣው ብሎ ከማሳተም፤ ወይም ከኔ በላይ አዋቂ . . . ከእኔ በላይ ደራሲ ላሳር ብሎ ከመጓዝ ግራ ቀኝ ማየት ተገቢ ነው። ብዙዎች ከጠፉበት ቤርሙዳ መዳንም ያስችላል።